August 08, 2026 ዜና (News)
  • 9
  • ቀድሞስ የክብር ባለቤት የጌታችን የመኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ኾነው እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ተሠውራባቸው እንዴት ዝም ብለው ይቀመጣሉ? ሁለት ሱባዔ ካደረሱ በኋላም የነገሩትን የማይረሳ፣ የለመኑትን የማይነሳ እግዚአብ…

    ቀድሞስ የክብር ባለቤት የጌታችን የመኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ኾነው እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ተሠውራባቸው እንዴት ዝም ብለው ይቀመጣሉ? ሁለት ሱባዔ ካደረሱ በኋላም የነገሩትን የማይረሳ፣ የለመኑትን የማይነሳ እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታቸውን ሰምቶ ነሐሴ ፲፭ ቀን የእመቤታችንን ሥጋ ሰጥቷቸው በክብር ገንዘው በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል፡፡ በሦስተኛው ቀንም እንደ ልጇ እንደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታለች፡፡ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጇ ትንሣኤ” ያሰኘውም ይህ ታሪክ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ሲሰብክ ቆይቶ ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ወደ ሰማይ ስታርግ አገኛት፡፡ በዚህ ጊዜ “ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ፤ ዛሬ ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁን?” ብሎ ትንሣኤዋን ባለማየቱ ሀዘን ስለ ተሰማው 140 ከደመናው ይወድቅ ዘንድ ወደደ፡፡ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” እንዲል፡፡ እመቤታችንም “አይዞህ አትዘን፤ ባልንጀሮችህ ሐዋርያት ያላዩትን ትንሣኤዬን አንተ አይተሃል” ብላ ከሙታን ተለይታ መነሣቷንና እንዲነግራቸው አዝዛ የያዘቸውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው፡፡ እርሱም ትዕዛዟን ተቀብሎ በክብር ከተሰናበታት በኋላ ወደ ሐዋርያት ሔዶ እንዳልሰማ እንዳላየ መስሎ “የእመቤታችን ነገር እንደምን ኾነ?” አላቸው፡፡ እነርሱም “አግኝተን ቀበርናት” ሲሉት “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይኾናል?” አላቸው፡ ፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚህ በፊት የክርስቶስን ትንሣኤ መጠራጠሩን ጠቅሶ እየገሠጸ ስለ እመቤታችን መቀበር እነርሱ የሚነግሩትን ኹሉ መቀበል እንደሚገባው ለቅዱስ ቶማስ አስረዳው፡፡ ቅዱስ ቶማስም የያዘውን ያውቃልና ጸጥ ብሎ ሲሰማው ቆየ፡፡ ቅዱስ ቶማስም “አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ አግኝቻታለሁ” ብሎ የሰጠችውን ሰበን ለሐዋርያት ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም በእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት እየተደሰቱ ሰበኑን ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩን በቅዳሴ ጊዜ ሠራዒ ዲያቆኑ በሚይዘው መስቀል ላይ የሚታሠረው መቀነት መሰል ልብስ፤ እንደዚሁም አባቶች ካህናት በመስቀላቸው ላይ የሚያደርጉት ቀጭን ልብስና በራሳቸው የሚጠመጥሙት ነጭ ሻሽ የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው፡፡ በዓመቱ ቅዱሳን ሐዋርያት “ቶማስ የእመቤታችን ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን?” ብለው ከየሀገረ ስብከታቸው ተሰባስበው ጌታችን ሥጋዋን እንዲሰጣቸው በጠየቁበት በዚሁ ወቅት ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ቢይዙ ጌታችን ልመናቸውን ተቀብሎ ነሐሴ ፲፮ ቀን እመቤታችንን መንበር፤ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፤ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ እመቤታችንንም ሐዋርያትንም አቍርቧቸዋል፡፡ እነርሱም እመቤታችንን በዓይናቸው ከማየት ባሻገር አብረው ሥጋውን ደሙን ተቀብለዋል /ትርጓሜ ውዳሴ ማርያም/፡፡ ይህንን ትምህርት መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ከነሐሴ ፩-፲፭ ያለው ሁለት ሱባዔ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ኾኖ በምእመናን ዘንድ መጾም እንደሚገባው ሥርዓት ሠርተውልናል /ፍት.ነገ.አን.፲፭/፡፡ ይህ ጾምም “ጾመ ማርያም (የማርያም ጾም)” ወይም “ጾመ ፍልሰታ ለማርያም (የማርያም የፍልሰቷ ጾም)” እየተባለ ይጠራል፡፡ ‹ፍልሰት› የሚለው ቃልም “ፈለሰ ሔደ፤ ተሰደደ” ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ አገር መሔድን ያመለክታል፡ ፡ ‹ፍልሰታ ለማርያም› ሲልም እመቤታችን 141 ቅድስት ድንግል ማርያም ካረፈች በኋላ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መወሰዷን የሚያስረዳ መልእክት አለው፡፡ በጾመ ፍልሰታ በቤተ ክርስቲያናችን በየቀኑ በማኅሌቱ፣ በሰዓታቱና በቅዳሴው በሚደርሰው ቃለ እግዚአብሔር ነገረ ማርያም ማለትም የእመቤታችን ከመጸነሷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ድረስ ያለው ታሪኳ፣ ለአምላክ ማደሪያነት መመረጧ፣ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ክብሯ፣ ርኅርራኄዋ፣ ደግነቷ፣ አማላጅነቷ፣ ሰውን ወዳድነቷ በስፋት ይነገራል፡፡ እመቤታችንን ከሚያወድሱ ድርሳናት መካከልም በተለይ ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌንና ነገረ ድኅነትን ከነገረ ማርያም ጋር በማዛመድ የሚያትተው ቅዳሴ ማርያም፤ እንደዚሁም ነገረ ድኅነትን ከምሥጢረ ሥጋዌ (ከነገረ ክርስቶስ) እና ከነገረ ማርያም ጋር በማመሣጠር የሚያትተው ውዳሴ ማርያምም በስፋት ይጸለያል፤ ይቀደሳል፤ ይተረጐማል፡፡ በሰንበታት የሚዘመሩ መዝሙራት፤ በየዕለቱ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለተዋሕዶ በእግዚአብሔር መመረጧን፣ ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን፣ ክብሯን፣ ቅድስናዋን፣ ንጽሕናዋን የሚያወሱ ናቸው፡፡ በጾመ ፍልሰታ ባሕታውያን ብቻ ሳይኾኑ ዓለማውያንም በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእመቤታችን አማላጅነት የሰይጣንን ፈተና ድል ለማድረግ እንዲቻላቸው ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በየገዳማቱና በየአብያተ ክርስቲያናቱ በዓት አዘጋጅተው፣ ሱባዔ ገብተው፣ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፡ ፡ እንደዚሁም ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ እኛም የእመቤታችንን ዕረፍትና ትንሣኤ በማሰብ ከልጇ ከወዳጇ የሚገኘውን ጸጋና በረከት ተስፋ በማድረግ የአባቶቻችንንና የእናቶቻችንን ፈለግ ተከትለን በየዓመቱ ጾመ ፍልሰታን እንጾማለን፤ የምንችል ደግሞ አስቀድሰን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እንቀበላለን፡፡ በተጨማሪም ይህ ጾም ለእመቤታችን ያለንን ፍቅርም የምንገልጽበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ ኦርቶዶክሳውያን ሕፃናት በአብዛኛው ትምህርተ ወንጌል የሚማሩት፤ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የሚቀበሉት በዚህ በጾመ ፍልሰታ ነው፡፡ ኹላችንም ጌታችን በስሙ ሁለትም ሦስትም ኾነን ለጸሎትና ለመልካም ሥራ ብንሰባሰብ እርሱ በመካከላችን እንደሚገኝ የገባልንን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ /ማቴ.፲፰፥፳/ በጾመ ፍልሰታ ሳምንታት በጌታችን፣ በእመቤታችንና በቅዱሳን ሐዋርያት ስም በቤተ ክርስቲያን ተሰባስበን ቅዱሳት መጻሕፍትን ከመማር ባሻገር ብንጾም፣ ብንጸልይ፣ ብናስቀድስ፤ እንደዚሁም ሥጋውን ደሙን ብንቀበል በበረከት ላይ በረከትን፤ በጸጋ ላይ ጸጋን እናገኛለን፡፡ በኋላም ሰማያዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንችላለን፡፡ ነገር ግን በሕግ የተከለከለ እስኪመስል ድረስ በዚህ ወቅትም ኾነ በሌላ ጊዜ ሥጋውን ደሙን የሚቀበሉ ወጣቶች ጥቂቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም አረጋውያንና ሕጻናት ብቻ ሳይኾኑ ወጣቶችም ጭምር የመቍረብና የመዳን ክርስቲያናዊ መብት እንዳለን በመረዳት ራሳችንን ገዝተን፣ ንስሐ ገብተን፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል ይገባናል፡፡ አምላካችን በማይታበል ቃሉ “ሥጋዬን የሚበላ፤ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው” በማለት ተናግሯልና /ዮሐ.፮፥፶፬/፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋና በረከት አይለየን።